የኢትዮጵያ እግር ኳስ በደጋፊዎች መካከል ለሚቀስቀስ ግጭት እና እርሱን ተከትሎ ለሚፈጠር ኹከት ባይተዋር ባይሆንም የቅርብ ጊዜ ክስተቶች ግን ከስፖርትም በዘለለ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ነባራዊ መልክ የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን ማስተዋል ይቻላል።
በ2009 ዓ.ም በርካታ ቁጥር ያለው የስቴዲየም ብጥብጥ በተለይም በላይኛው ፕሪሚየር ሊግ ቢዘገብም ከብጥብጦቹ ጀርባ እግር ኳስን የሚሻገሩ ገፊ ምክንያቶች እምብዛም እንዳልነበሩ ይጠቀሳል።
በያዝነው ዓመት በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚለኮሱ ግጭቶች እና ረብሻዎች ቁጥር አይሏል።
ከተጀመረ ጥቂት ሳምንታትን ብቻ ባስቆጠረው የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ከረብሻዎች ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ክለቦች ላይ የጣለው ቅጣት ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደደረሰ ጉዳዩን የሚከታተሉ ባለሞያዎች ያስረዳሉ።
መጠናቸው ይለያይ እንጅ ባለፉት ሁለት ወራት ሃዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ አዲግራት፣ ጅማ እና በቅርቡ ደግሞ ወልዲያ ከተሞች ውስጥ ግጭቶች እና ረብሻዎችን አስተናግደዋል።
ባለፈው እሁድ በወልዲያ ስፖርት ክለብ እና በመቀሌ ከተማ መካከል ሊደረግ የነበረው የእግር ኳስ ጨዋታ ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ህይወት የጠፋ ሲሆን ንብረት ላይ ዘረፋና ወድመት ተከስቷል።
በዕለቱ ማገባደጃ ላይ በመቀሌ ከተማ መንገዶች ላይም ክስተቱን ለመቃወም በርካታ ሰዎች ወጥተው ነበር። ጨዋታው ካለመካሄዱ በተጨማሪ የግጭቱ አሻራ እስከቀጣይ ቀናት ቀጥሏል።
የትግራይ ክልል የእግር ኳስ ፈዴሬሽንም ክስተቱን በማውገዝ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈደሬሽን ጉዳዩን ኣጣርቶ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ በደብዳቤ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ የወልዲያው ክስተት ከእግር ኳስ የሚሻገር ገፅታ እንዳለው ይገልፃሉ።
በሴካፋ ውድድር ከሚሳተፈው የወንድ አዋቂዎች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ጋር ናይሮቢ የሚገኙት አቶ ጁነዲን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ግጭቱ ከስፖርት ሜዳ ውጭ መቀስቀሱን አስታውሰው “ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ይዘት ያለው ነገር ነው። ሜዳ ውስጥ ቢሆን ከኳስ ድጋፍ ጋር ይያያዝ ነበር፤ ሌላ ትኩሳት ያለበት ነው የሚመስለኝ፤ እግር ኳስ ብቻውን አይመስለኝም” ሲሉ ተናግረዋል።
ከማኅበረሰባዊነት እስከ ብሔረተኛነት
በስፖርቱ ዓለም የተመልካቾች ነውጠኛነት ምክንያቶች ብዙ ናቸው ሲል የሚያስረዳው የስፖርት ተንታኙ መንሱር አብዱልቀኒ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ወይንም ምጣኔ ኃብታዊ ብሶቶች ስቴዲየም ላይ ሊያጠሉ እንደሚችሉ ይናገራል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስን የታከከ ብጥብጥ ሲከሰት “የመጀመሪያው ባይሆንም እየተባባሰ ግን ሄዷል። የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን ስናጤን ደግሞ ከእግር ኳስ ባሻገር ሌሎች የጀርባ ምክንያቶች እንዳሉ ግልፅ ነው”ይላል።
እግር ኳስ ማኅበረሰባዊ መሰረት ከሌለው በስተቀር የጠነከረ የእኔነት ስሜት ሊፈጥር አይቻለውም የሚለው መንሱር፤ ይሁንና ክለቦች ከማኅበረሰባዊ መሰረታቸው በዘለለ ብሔር ተኮር መልክን እየተላበሱ የመምጣታቸውን አዝማሚያ “አደገኛ ነው” ይለዋል።
“ከአንዳንድ በጥባጭነት እጅግ ወደተደራጀ ነውጠኛነት ሊሄድ ይችላል። ቀስ በቀስ ወደመቧደን እየተሄደ ነው። ራሳችንን መከላከል እና ማዘጋጀት አለብን በሚል ደጋፊዎች ራሳቸውን ማደራጀት ከጀመሩ የሚያሰጋ ዓይነት እውነታ ሊፈጠር ይችላል።”
ላለፉት ሁለት ዓመታት መቀሌ ከተማ የእግር ኳስ ክለብን የደገፈውና ባለፈው እሁድ ማለዳ የወልዲያ አመሻሹን ደግሞ የመቀሌ ኹከቶችን የታዘበው ገብረመድህን ኃይለስላሴ በዚህ አስተያየት ይስማማል።
“የእኔነቱ መንፈስ ከርሮ ከኳስ ወዳጅነት ወደብሔርተኝነት ነው እየሄደ ያለው፤ ከዚህ ቀደም ብጥብጡ ተጀምሮ የሚያልቀው ስቴዲየም ነው፤ ከዚያ አያልፍም። አሁን አሁን እየታየ ያለው ግን የባሰ ነው” ሲል ለቢቢሲ አስተያየቱን ሰጥቷል።
የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ክለብን የሚደግፈውና የድጋፍ እንቅስቃሴዎችን በማስተባበር ተሳትፎ ያለው እሸቱ ቢያድጎ በአንፃሩ ስለ ክለብ ድጋፍ ፖለቲካዊ አንድምታዎች የሚሰጡ አስተያየቶች የተጋነኑ ናቸው ባይ ነው።
“ሰዎችን ወደሜዳ የሚስባቸው በዋናነት ኳሱ ነው” በማለት እሸቱ ይናገራል።
ሆኖም ክለቦች የማንነት ማግነኛ እና የራስ ኩራት መገለጫ መድረኮች እየሆኑ የመምጣታቸውን ሃቅ በየአካባቢው እየጎመራ ከመጣው የዘውግ ብሔርተኛነት ጋር የሚያስተሳስሩት አልጠፉም።
እሸቱ የሚደግፈው ፋሲል ከነማ ለምሳሌ ስያሜውን ከክለቡ መናገሻ ጎንደር ከተማ መስራች አፄ ፋሲል ጋር ሲያሰናስል በአርማው ደግሞ በአፄ ቴዎድሮስ ምስል አሸብርቋል።
ፋሲል ከነማ ከአካባቢው የአለባበስ ልማድ እንደሆነ ከሚነገርለት ጃኖ የማልያ እሳቤውን እንደተዋሰ የሚናገረው እሸቱ ከደጋፊ አመራሮች ጋር በመሆን በመሰንቆ የሚታጀብ የአደጋገፍ ስልትን ተግባራዊ ለማድረግ በመሥራት ላይ መሆኑንንም ይገልፃል።
ይህ ታሪክን የማጣቀስ ሁኔታም በጅማም ታይቷል።
ከዚህ ቀደም ጅማ ከነማ ይባል የነበረው የእግር ኳስ ክለብ በአዲስ መልክ ሲዋቀር በታሪካዊው ንጉሥ ስም ጅማ አባጅፋር የተሰኘ አዲስ መጠሪያን ተላብሷል።
ክለቡን ለበርካታ ዓመታት የደገፈውና በአካባቢው ተወልዶ በጅማ ከተማ ያደገው ገዛኸኝ ከበደ ይህ እርምጃ ከከተማዋ ነዋሪዎች ባሻገር ከሌሎች በርካታ የአካባቢው ወረዳዎች ደጋፊዎችን ለመሰብሰብ ታልሞ የተከናወነ ነው ይላል።
የአባ ጅፋር ደጋፊዎች ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከሀዋሳ ከነማ ጋር በነበረው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ረብሻ አስነስተዋል በሚል ክለቡ አንድ ጨዋታን ያለደጋፊ እንዲያከናውን፤ እንዲሁም 150 ሺህ ብር እንዲከፍል ቅጣት ተላልፎበታል።
ገዛኸኝ እንደሚለው ለረብሻው መንስዔ የሆነው ሌላኛው የከተማዋ ክለብ ጅማ አባ ቡና ላይ ያልተገባ በደል እንደደረሰበት በመታመኑ ነው።
“የፌዴሬሽን ሰዎች ለኦሮሚያ ክልል ክለቦች ጥሩ አመለካከት የላቸውም ይባላል” ሲል ገዛኸኝ ተናግሯል።
በኦሮሚያ ውስጥ የፌዴራል ስፖርት ተቋማትን በጥርጣሬ መመልከት በእግር ኳስ ብቻ ሳይገደብ አትሌቲክስ ላይም ይስተዋል እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ከዚህ በኋላስ?
አቶ ጁነዲን የሚመሩት ፌዴሬሽን ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲኖር ከክልል መንግሥታት እና ከተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ ይናገራሉ።
“እግር ኳስ ከፖለቲካ፣ ከኃይማኖትና ከዘር የፀዳ መሆን እንዳለበት የሚያስረዳውን ዓለም አቀፍ መርኅ መተግበር እንዳለበት እናምናለን” ብለዋል።
በእግር ኳስ ተመልካቾች ነውጠኝነት ላይ ጥናትን ላከናወነው መንሱር ግን ፌዴሬሽኑ ከውይይት የዘለለ ፋይዳ ያለው ነገር እየሰራ አይደለም።
ክለቦች ሲቋቋሙ ወይንም ሲዋቀሩ አካባቢያዊ መገለጫ ወይንም ከተማዊ ስያሜ ሊኖራቸው ቢችልም ከብሔር፣ ከዘር ወይንም ከኃይማኖት ጋር በተቆራኘ መልኩ መደራጀት ክልክል መሆኑን የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ማኅበራት ማደራጃ መመሪያ አንቀፅ 50 ቁጥር 2 ይገልፃል።
ነገር ግን ባለፈው ዓመት ብቻ ፌዴሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ሊጎች የብሔር ስም የተቀጠላላቸው 14 ክለቦች ውድድር ያደርጉ ነበር።
ከእነዚህ ክለቦች መካከል ሐድያ ሆሳዕና የእግር ኳስ ክለብ፣ ወላይታ ድቻ፣ ጎፋ ባሬንቼ፣ ካብዳባ አፋር የመሳሰሉ ክለቦች እንዳሉ መንሱር ይገልፃል።
ከዚህም በተጨማሪ ክለቦች የተለያዩ የአገሪቱን ክልሎች እንደሚወክሉ መታሰቡ፤ ክልሎች ብሔርን መሰረት አድርገው እንደመዋቀራቸው ብሄርን እንደሚወክሉ ወደመታሰብ አድጓል።
መጠሪያው ባይኖርም እንኳን ከሚመጡበት ክልል ጋር ተያይዞ የእገሌ ብሔር ነው የሚል እምነት አሳድረዋል።
እግር ኳስ ይብቃን?
ገብረመድህን አደጋገፍ አሁን ባለው መልኩ የሚቀጥል ከሆነ እግር ኳሱ ከናካቴው ቢቀር ይሻላል ባይ ነው። “ያው እንደለመድነው የአውሮፓ እግር ኳስን ብንከታተል ይሻለናል” ይላል።
መንሱር የእግር ኳሱን ሊጎችን ሙሉ በሙሉ ማቆም ችግሮች አልፈታ ካሉ ሊደረስበት የሚችል እርምጃ እንደሆነ ይናገራል።
ለአሁኑ ግን ሁሉም ጨዋታዎች እኩል እንዳልሆኑ ግንዛቤ ተወስዶ የስጋት መጠን ልኬት ሊወጣላቸው ይገባል በማለት ምክሩን ይለግሳል።
በዚህም መሰረት አደጋ የመፈጠር ዕድላቸው ከፍ ያሉባቸው ጨዋታዎችን በባዶ ሜዳ ከማጫወት በሌላ ሜዳ እስከማጫወት ድረስ የሚሄድ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል መንሱር ይጠቁማል።
ለዘለቄታው መፍትሄ ለማበጀት ግን ሊጎች በተለይም ፕሪሚየር ሊጉ የሚካሄድበትን መዋቅር ከአገሪቱ ነባራዊ እውነታ ጋር በተናበበ መልኩ ማስተካከል ያሻል ባይ ነው።
እግር ኳስ ብቻውን አገርን ለመበታተን የሚያበቃ አቅም የለውም ሲል የሚሟገተው መንሱር በአግባቡ ከተያዘ የአንድነትን፣ የወንድማማችነትን ስሜት እንደሚያዳብር አፅንዖት ሰጥቶ ይናገራል።
“ነገር ግን ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ የባሕርይ ለውጦች፣ ችግሮች እና ክፉ አስተሳሰቦች ሁሉ በስቴዲየም ይገለፃሉ” ይላል።
ምንጭ: ቢቢሲ