ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በግብፅ ፓርላማ ተገኝተው ለአገሪቱ ሕዝብና ለፓርላማ አባላት ንግግር እንዲያደርጉ የተያዘውን ፕሮግራም ለማስቆም፣ የግብፅ ፓርላማ ተወካዮች የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰባቸውን መረጃዎች አመለከቱ፡፡

የአገሪቱ ፓርላማ አባል በሆኑት አብደልሃሚድ ከማል አነሳሽነት የተጀመረው የተቃውሞ መግለጫ ላይ ሌሎች 18 የፓርላማው ተወካዮች እንደፈረሙ፣ የተቃውሞ መግለጫውም ለፓርላማው አፈ ጉባዔ  አሊ አብደል አል እንደቀረበ የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በታኅሳስ ወር በግብፅ ሊያደርጉት ያቀዱት ይፋዊ የሥራ ጉብኝትን፣ እንዲሁም ለፓርላማ አባላት ንግግር እንዲያደርጉ የተያዘውን ዕቅድ እንደሚቃወሙ የፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብፅ ላይ ጫና ለመፍጠር በተገኙባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች በሙሉ የማያደርጉት ጥረት የለም፤›› ሲሉ የፓርላማ አባላቱ በተቃውሞ መግለጫቸው ማስፈራቸውንም የግብፅ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን የጉብኝት ዕቅድንና የፓርላማ ንግግር የግብፅ ፓርላማ አባላት የተቃወሙት፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረው ድርድር በመስተጓጎሉና ግድቡ የግብፅን የውኃ ድርሻ ይቀንሳል ከሚል መነሻ ነው፡፡

‹‹የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትር የጉብኝት ዕቅድ የምንቃወመው የዓባይ ውኃ ጉዳይ፣ የግብፅ ብሔራዊ ደኅንነት መሠረታዊ አካልና የማይታለፍ ቀይ መስመር በመሆኑ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምትገነባው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ ቆይቶ የተሰናከለውን ድርድር አስመልክቶ የአገሪቱ የእርሻና መስኖ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ብሔራዊ የባለሙያዎች ቡድን በፓርላማ ቀርበው እንዲያስረዱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በታኅሳስ ወር በግብፅ የሚያደርጉት የሥራ ጉብኝት በፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ጥያቄ መሠረት መሆኑንና እስካሁን የፕሮግራሙ ይዘት አለመቀየሩን ገልጸዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ የአካባቢ ተፅዕኖና የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅን፣ እንዲሁም የሚካሄደው ገለልተኛ ጥናት መሠረት የሚያደርግባቸው መረጃዎችን በተመለከተ ግብፆች ያቀረቡትን መከራከሪያ ኢትዮጵያ አልተቀበለችም፡፡

በግብፅና በሱዳን መካከል የተፈረመው የቅኝት ግዛት ዘመን የውኃ ክፍፍል ስምምነት፣ ኢትዮጵያን የማይመለከት መሆኑን ባለሥልጣኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዓባይ ትብብር ማዕቀፍን ኢትዮጵያና ሌሎች አገሮች ተስማምተው በሕግ አውጪ ተቋሞቻቸው ሕግ አድርገው አፅድቀውና የቅኝ ግዛት ስምምነትን ውድቅ አድርገው ሳለ፣ እ.ኤ.አ. ወደ 1959 የቅኝ ግዛት ስምምነት መመለስ ኢትዮጵያ በቀናነት ለምታደርገው ድርድር ክብር አለመስጠት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የተፈረመውን የመርህ መግለጫ ስምምነት እንደሚጣረስም አስረድተዋል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ስምምነት ግብፅ ለመጀመርያ ጊዜ የላይኛው የተፋሰሱ አገሮች ጉልህ ጉዳት ሳያደርሱ ውኃን የመጠቀም መብት እንዳላቸው ተቀብላ መስማማቷን ባለሥልጣኑ በዋቢነት ጠቁመዋል፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲን ጨምሮ የተለያዩ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ‹‹የግብፅ የውኃ ድርሻን ምንም መንካት አይቻልም፣ ጠብታም እንኳ ቢሆን፤›› የሚሉና ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው መግለጫዎችን እያወጡ ይገኛሉ፡፡

ዓለም አቀፍ የውኃ ደኅንነት ባለሙዎች በበኩላቸው፣ ግብፅ በከፍተኛ የመንግሥት መዋቅር ደረጃ ድርድሩ እንዲቀጥል ከማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሌላት ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ አሁንም አለመግባባቶችን በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን እየገለጹ ሲሆን፣ የግድቡ ግንባታ ግን የሚቆመው ሲጠናቀቅ ብቻ መሆኑን በግልጽ ይፋ አድርገዋል፡፡

ምንጭ: ኢትዮጵያን ሪፖርተር