ከአበቅየለሽ-እስከ-ፎር-ሲስተርስ.jpg
ከአበቅየለሽ-እስከ-ፎር-ሲስተርስ.jpg

‹‹ጨዋ ሰፈር›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው መንደር ጎንደር ውስጥ ከሚገኙ ጥንታዊ መኖሪያ አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የቦታ ስያሜ የሚሰጠው በምክንያት እንደመሆኑ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችም ለሰፈሩ የሰጡትን ስም ምክንያት ያብራራሉ፡፡ በአካባቢው ከሚኖሩ ሰዎች አብዛኞቹ የተረጋጋ ሕይወት የሚመሩ እንደሆኑ ስለሚታመን ስሙ እንደተሰጠ ይነገራል፡፡ ሰፈሩ ፀጥ ያለና የሰከነ በመሆኑ ለኑሮ የተመቸ እንደሆነም ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡

ሰፈሩን በጎበኘንበት ወቅት እንዳስተዋልነውም፣ አካባቢው ግርግር አይበዛበትም፡፡ ከመንገድ ዳርቻ ወጣ ብለው የተሠሩት ቤቶች ጽሞና፣ አካባቢው ለመኖሪያነት ታስቦ መሠራቱን ይጠቁማሉ፡፡ እንደ ‹‹ጨዋ ሰፈር›› ያሉ መንደሮች በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ያላቸውን ቦታ ያህል በጎብኚዎች ዘንድ አይታወቁም፡፡ በየአገር ውስጥም ይሁን በውጭ ቱሪስቶች በብዛት ሲጎበኙም አይስተዋልም፡፡ ጎብኚዎች እንደ ጎንደር ወዳሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ሲሄዱ ብዙውን ጊዜ የሚጎበኙት ታዋቂ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ አካባቢዎችን ነው፡፡

የማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት የሚንፀባረቅባቸው አካባቢዎች በጉብኝት ወቅት ብዙም ትኩረት ሲሰጣቸው አይስተዋልም፡፡ ሆኖም ማኅበረሰቡ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ያሳያሉ፡፡ መኖሪያ መንደሮች፣ መዝናኛ ቦታዎችና የገበያ ማዕከሎች የማኅበረሰቡ የዘወትር ኑሮ ከሚታይባቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ጎንደር ከሚገኙ መዝናኛ ቦታዎች ቀደምቱን አበቅየለሽ ጠጅ ቤትና የቅርብ ጊዜውን ፎር ሲስተርስ ሬስቶራንት ማነጻጸር ይቻላል፡፡ አበቅየለሽ ጠጅ ቤት ለበርካታ ዓመታት የጎንደር ነዋሪዎችና ለከተማዋ እንግዳ የሆኑም የተስተናገዱበት ጠጅ ቤት ነው፡፡ በአንፃሩ ፎር ሲስተርስ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ፣ መጠጥ፣ አለባበስና ሙዚቃ ለማስተዋወቅ የተከፈተ ዘመነኛ ሬስቶራንት ነው፡፡

አበቅየለሽ ጠጅ ቤት ከጎንደር ንግድ ምክር ቤት መሥራቾች አንዷና የመጀመርያ ሥራ አስፈጻሚ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የእማሆይ አበቅየለሽ ይመር ይዞታ ነው፡፡

አበቅየለሽ ጠጅ ቤት ከጎንደር ንግድ ምክር ቤት መሥራቾች አንዷና የመጀመርያ ሥራ አስፈጻሚ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የእማሆይ አበቅየለሽ ይመር ይዞታ ነው፡፡ ጠጅ ቤቱን በጎበኝንበት ወቅት ያገኘናቸው ወንድማቸው አቶ ታረቀኝ ሞላና ሌሎችም ቤተሰቦቻቸውን ነበር፡፡ እማሆይ አበቅየለሽ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም፣ ጠጅ ቤቱ አሁንም አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡

የ81 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አቶ ታረቀኝ እንደሚናገሩት፣ አበቅየለሽ በጠጅ ዝናን ያተረፈ ቤት ነው፡፡ ‹‹ጠጁ በጣም ልዩ ስለሆነ ከባለሥልጣኖች እስከ መደበኛ ሰው ይመጣ ነበር፤›› ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡ አንድ ብርሌ ጠጅ በአንድና በሁለት ብር ከሚሸጥበት ጊዜ ጀምሮ ጠጅ ቤቱ ብዙዎችን ማስተናገዱን ይናገራሉ፡፡ ስለ ጠጁ እንዲሁም ስለ እማሆይ አበቅየለሽም ብዙ እንደተዘፈነና ቅኔም እንደተዘረፈም ያክላሉ፡፡

‹‹ቀድሞ ወደ አበቅየለሽ ድፍን ጎንደር ይመጣል፡፡ አሁን እንኳን ብዙ ጠጅ ተከፍቷል፤›› ይላሉ፡፡ ፍሪዳ ተጥሎ፣ ጠጅ እየተጠጣ፣ የአዝማሪዎች ቅኔ አዘል ሙዚቃ የሚደመጥበትን ዘመንም ያስታውሳሉ፡፡ እማሆይ አበቅየለሽ ከቤተሰቦቻቸው የተማሩትን ጠጅ አጣጣል ለእህትና ለወንድም ልጆቻቸውም አስተምረዋል፡፡ የአቶ ታረቀኝ የልጅ ልጅ የ22 ዓመቷ ቅድስት፣ ‹‹ብዙ ባልችልም እኔም የጠጅ አሠራር ተምሬያለሁ፤›› ትላለች፡፡ በሷ ዘመን ጠርሙስ ጠጅ በ80 ብር ይሸጣል፡፡

እንደ ትሪፕአድቫይዘር ባሉ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ድረ ገጾች እውቅና የተሰጠው ፎር ሲስተርስ፣ የጎንደርን የአሁን ገጽታ የሚያሳይ ሬስቶራንት ነው፡፡ ወደ ሬስቶራንቱ የሄደ ሰው ጡሩምባ እየተነፋ ከበር ጀምሮ አቀባበል ይደረግለታል፡፡ ወደ ሬስቶራንቱ ከገባ በኋላም የክብር ካባ ይደረብለትና ይስተናገዳል፡፡

ፎር ሲስተርስ የተከፈተው በአራቱ እህትማማቾች ጤና ሥራው፣ ሔለን ሥራው፣ ሰናይት ሥራውና ኤደን አጥናፉ ጥምረት ከስድስት ዓመት በፊት ነው፡፡ ከመሥራቾቹ አንዷ ሰናይት እንደምትናገረው፣ ተስተናጋጆች ወደ ሬስቶራንቱ ከሚገቡት ቅጽበት ጀምሮ በባህላዊ መንገድ ይስተናገዳሉ፡፡ ዶሮ ወጥና ሌሎችም ባህላዊ ምግቦች እንዲሁም ባህላዊ መጠጦችም ይቀርባሉ፡፡

የሬስቶራንቱ አስተናጋጆች ባህላዊ ልብስ ይለብሳሉ፡፡ አመሻሽ ላይ ደግሞ አዝማሪዎች ሙዚቃ ያስደምጣሉ፡፡ ባህላዊ ውዝዋዜም ይቀርባል፡፡ ሰናይት እንደምትለው፣ ሬስቶራንቱ በአገርና ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ድረ ገጾች ላይ መመስገኑ የተስተናጋጆችን ቁጥር ጨምሮታል፡፡ ሰዎች ባህልን በከፊልም ቢሆን የሚመለከቱበት መርሐ ግብር በማቅረብ በሬስቶራንቱ ቆይታቸውን የማይረሳ ለማድረግ እንደሚሞክሩም ታስረዳለች፡፡

ከተማዋን ለዓመታት ያስጎበኘው አሰግድ ተጠቃሽ ከሆኑ መንደሮች መካከል ቀድሞ የቤተ እስራኤላውያን መኖሪያ የነበረውን ወለቃ መንደር፣ ወለቴ መንደርና ዋላጅ መንደር ያነሳል፡፡

በሌላ በኩል የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹልን፣ የጎንደር ገበያ ሰኞና ቅዳሜ ይከናወናል፡፡ በተለይ የቅዳሜ ገበያ የሞቀ ሲሆን፣ የተለያየ መንደር ነዋሪዎች በኅብረት ይገበያዩበታል፡፡ ከተማዋን ለዓመታት ያስጎበኘው አሰግድ ተጠቃሽ ከሆኑ መንደሮች መካከል ቀድሞ የቤተ እስራኤላውያን መኖሪያ የነበረውን ወለቃ መንደር፣ ወለቴ መንደርና ዋላጅ መንደር ያነሳል፡፡

የቀድሞ የጣልያን ወታደሮች መኖሪያ የነበረው ሰፈር አምባላጅ ይባላል፡፡ በንጉሥ ግራ ቀኝ በሚቀመጡ ባለሥልጣኖች የተሰየሙ ግራ ወንበርና ቀኝ ወንበር የሚባሉ መንደሮችም በታሪክ ይወሳሉ፡፡ ቀደም ባለው ዘመን ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ጎንደር የሚሄዱ ሰዎች የሚሰፍሩበት ግራ ጎንደር የሚባል መንደርም ነበር፡፡ በእነዚህ መንደሮች ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ለሰፈሮቹ እውቅና የድርሻቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

አስጎብኚው እንደሚለው፣ በዘመነ ጎንደር ታሪክ ከማይዘነጉ ታላላቅ ሰዎች መካከል ባለቅኔው ተዋነይ አንዱ ነው፡፡ ጸሐፌ ትዕዛዝ ሺኖዳ በታሪክ ጽሑፎቻቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ባለቅኔው ሊቅ ክፍሌ እንዲሁም የደብረ ብርሃን ሥላሴ ግድግዳ ላይ ያሉ ሥዕሎችን እንደሠሩ የሚነገርላቸው አባ ኃይለመስቀልና በጎንደር ኪነ ሕንፃ ታዋቂ የሆኑት አባ ገብረክርስቶስም ይገኙበታል፡፡

ጎንደር ውስጥ የብዙዎች የቅርብ ዘመን ትውስታ የሆኑ አባባ ደመናው የሚባሉ የኔቢጤ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ መላ ሕይወታቸውን በድህነት ቢያሳልፉም፣ በንግግራቸው ታዋቂ ነበሩ፡፡ ማኅበረሰባዊ መስተጋብርን በሚተቹ አስተያየቶች የሚታወቁ ሲሆን፣ ዛሬም ድረስ የተናገሯቸው ነገሮች ይወሳሉ፡፡ በተመሳሳይ ፒያሳ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ አንድ ልብስ ሰፊም በሰላ ትችታቸው ይታወቃሉ፡፡

የንግድ እንቅስቃሴ መስመርን ተመርኩዛ የተቆረቆረችው ከተማዋ ውስጥ ለዘመናት ካገለገሉ የመገበያያ ቦታዎች በተቃራኒው ዘመነኛ ገጽታ የተላበሱ መገበያያዎች ተስፋፍተው ይታያሉ፡፡ ተዘዋውረን የጎበኘናቸው መገበያያ ማዕከሎች አልባሳት፣ የቤት ውስጥ መገልገያዎችና ሌሎችም ቁሳቁሶች ይሸመቱባቸዋል፡፡

መኖሪያ መንደሮች፣ መገበያያ ስፍራዎችና መዝናኛ ቦታዎች፣ የአንድ ማኅበረሰብን የዕለት ከዕለት ሕይወት በማሳየት ረገድ ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ አበቅየለሽ ጠጅ ቤትና በአንፃሩ ፎር ሲስተርስ ሬስቶራንትን ስንጎበኝ በዘመን ሒደት ያለውን ለውጥ ተመልክተናል፡፡ በተመሳሳይ ጥንት የተቆረቆሩ መንደሮችና በቅርብ ጊዜ ሰፈራ የተጀመረባቸው አካባቢዎች መካከልም በዘመን ልዩነት የተፈጠረውን የአኗኗር ዘዬ ለውጥ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በዋና ዋና የከተማዋ መገበያያ አካባቢዎች ካስተዋልነው መካከል የሴት ባጃጅ ሹፌሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ የፋሲል ግንብን ጨምሮ የተለያዩ የከተማዋ ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎች የተቀረፀባቸው የዕደ ጥበብ ውጤቶች በመገበያያ ቦታዎች በስፋት ከሚሽጡ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የታሪካዊ ቅርሶች ምስል ያለበት ቦርሳ፣ ስካርፍ፣ ረከቦት፣ ወንበርና ሌሎችም ቁሳቁሶችም ይሸጣሉ፡፡

እነዚህ አካባቢዎች በስፋት አለመተዋወቃቸውን አሰግድ ይናገራል፡፡ የሚዳሰሱ ቅርሶች በሚተዋወቁበት መጠን የማይዳሰሱ ቅርሶች ካለመተዋወቃቸው ባሻገር፣ ተገቢውን ጥበቃ በማግኘት ረገድም ክፍተቶች እንዳሉ ያስረዳል፡፡ ‹‹ቅርሶቹ ሲጎበኙ ሕይወት ያለው ነገር ጎን ለጎን አይቀርብም፤›› ይላል፡፡

ጎብኚዎች እንደ ‹‹ጨዋ ሰፈር›› ያሉ መኖሪያ መንደሮችን አልያም ከተማዋ ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው ስትሸጋገር ያለውን ሒደት የሚያሳዩ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ቢደረግ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም ይቻላል፡፡ ከሚዳሰሱ ቅርሶች በተጨማሪ፣ ልዩ ልዩ ማኅበረሰባዊ ክንውን የሚገለጽባቸው የማይዳሰሱ ቅርሶችንም ለጎብኚዎች ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የማኅበረሰቡ አኗኗር በቅርበት የሚታይባቸው ስለሆኑ ጎብኚዎችን በመሳብ፣ ከቱሪዝም ተጨማሪ ገቢ ለማግኝትም ያስችላሉ፡፡

‹‹የኅብረተሰቡ ባህል የሚታይባቸው መንደሮችን እንዲሁም እንደ ጠላ ቤትና ጠጅ ቤት ያሉትን ለጎብኚዎች ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም የሚተዋውቁት የፋሲል ግንብን የመሰሉት ብቻ ናቸው፤›› በማለት ይገልጻል፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ቢተዋወቁ፣ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ከማራዘም ጎን ለጎን ቅርሶቹ እንዲጠበቁ በማድረግ ረገድም አስተዋፅኦ እንዳለው ያስረዳል፡፡

ምንጭ: ኢትዮጵያን ሪፖርተር